ክብርት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)

የቢሮ ኃላፊ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ

ውድና የምትፈቀሩ የዚህ ድረገጽ ጎብኚዎቻችን፣

ምድረቀደምት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያና ለዓለም ህዝቦች ሁሉ ብሩህ መዲና በሆነችው ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ወደሚገኙ እጅግ ድንቅ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ስፍራዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ስል እጅግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በዚህ ወቅት አዲስ አበባ በበርካታ ምክንያቶች መጎብኘት የሚገባት ናት፡፡ ለምሳሌ፣ ቱሪስቶች በሰላም የሚቆዩባት ወይም ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለመጓዝ የጉዞ ዕቅድ የሚያወጡባት አስተማማኝ ሥፍራ ናት፡፡ እጅግ የቀነሰው የከተማዋ የወንጀል ምጣኔ፣ እጅግ ድንቅ ከሆነው የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይነት ጋር ሲደመር፣ ሁልጊዜ ምሉ በሙሉ አስተማማኝና ሰላማዊ የሆነ አየር በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚፈጥር ነው፡፡ በተጨማሪም፣ አዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ኪነጥበባዊ፣ ታሪካዊ፣ እሳቤያዊ እና ስነልሳናዊ የሆኑ የህዝቦች የብዝሃነት መገለጫዎችን በሚገባ ያቀፈች የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን የምትስብ ግሩም ማግኔት ናት፡፡ ይህም ሃቅ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የዕለታዊ አኗኗር አካል የሆነና የኢትዮጵያን እና የውጭ አገር የምግብ አሰራርን፣ የቢዝነስ ፈጣን እንቅስቃሴን እንዲሁም ቱሪስቶች አብዛኛውን ጊዜ በካዛንቺስ፣ ፒያሳ፣ ቦሌና በመሳሰሉት ቦታዎች የሚያጣጥሙትን እጅግ ማራኪ ለዛ ያለውን በታላቅ ደስታ የታጀበ የምሽት ህይወት የሚያካትት ነው፡፡ ... በቅርቡ በከተማችን ከተከፈቱት ማራኪዎቹ የአንድነት ፓርክ፣ የእንጦጦ ፓርክ እና የወዳጅነት ፓርክ በተጨማሪ፣ ለአብዛኛዎቹ ቱሪስቶች ላቅ ያለ ፋይዳ ያለው ሃቅ አዲስ አበባ ለሰው ልጆች እጅግ ውድ ከሆኑ የአርኪዮሎጂና የታሪክ ሃብቶች ጥቂቶቹን አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም እና መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው አዲስ አበባ ሙዚየምን በመሳሰሉ ሙዚየሞችዋ የያዘች መሆንዋ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ፣ ቱሪስቶች ታሪካዊ በሆኑ ህንፃዎች፣ ሃውልቶች፣ አብያተክርስቲያናት እና መስጊዶች እንዲሁም በከተማዋ ነዋሪዎች በሰላም ተቻችሎ የመኖር ባህል እጅግ እንደሚደሰቱ ከፍተኛ እምነት አለኝ፡፡ በእርግጥ፣ አዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊ፣ ስነልሳናዊ፣ እሳቤያዊና ታሪካዊ የሆኑ ምስጢራዊ ሥፍራዎች እና በተለይም ክርስቲያኖችና የእስልምና ተከታዮች ፈጣሪያቸውን ለዘመናት በእምነት ቦታዎቻቸው ሲያመልኩ፣ ሰው ሰራሽ በሆነ አጥር ብቻ ተለያይተው እንደ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል እና አንዋር መስጊድ ባሉ ቦታዎች የሚገኙባት ግሩም ህብር ያላት መዲና ናት፡፡ ከዚሁ ጋር እኩል ፋይዳ ያለው ነገር አዲስ አበባ ለበርካታ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫ መሆንዋ ነው፡፡ እነዚህም ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያሏቸውን ለረጅም ጊዜ የቆዩ የሁለትዮሽና ባለብዙ ፈርጅ የሆኑ መስተጋብሮች በኢትዮጵያና ተቀረው የዓለም ክፍል ያሉ ግንኙነቶችን በአብዛኛው ምሳሌ በሚሆን መንገድ አጠናክረዋል፡፡ በመጨረሻም፣ ጎብኚዎቻችንን የአፍሪካ ብሩህ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ወደሚገኘው ማራኪ የባህል፣ የኪነጥበብና የቱሪዝም መስህቦች ህብር እንኳን ደህና መጣችሁ ከማለት በተጨማሪ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ጥረቶችን በተመለከተ የሚሰሩ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት፣ የከተማችንን ልዩ ልዩ የልማት ተግዳሮቶች በስኬት ለመቅረፍ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ፕሮጀክቶችን በመንግስትና በግል ዘርፍ ትስስር ሞዴል እንዲያመነጩና እንዲተገብሩ የሚያበረታታ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ባለድርሻ አካላቶቻችን በአዲስ አበባ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን፣ ለምሳሌ፣ በዚህ ድረገጽ የተጠቀሱ አድራሻዎቻችንን በመጠቀም፣ የቢሮአችንን የቀጣይ አስር ዓመታት ስትራተጂክ ዕቅድ በሚገባ ማጥናት ይችላሉ፡፡ ከዛም በኋላ፣ ቢያንስ ኩባንያዎች አብረዋቸው ከሚሠሩ የትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች፣ የገበያ ጥናት በማካሄድ በርካታ የቱሪዝም ሥራዎችን የሚያቀርቡ የቢዝነስ ኩባንያዎችን መክፈት ይችላሉ፡፡ ይህም ሲጠናቀቅ፣ በእርግጥ፣ ሁላችንም በጋራ ጥረቶቻችን ስኬታማ እንሆናለን፡፡ አብረን፣ ሁልጊዜ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ እስከዛሬ ያሉን ዝናዎች የሚረጋግጡትም የጋራ ጥረቶቻችን በአዲስ አበባ የዘላቂ ቱሪዝም ፕሮጀክቶች በንድፈሃሳባዊና ተግባራዊ ጉዳዮች የሚታዩ ለውጦችን ማምጣታቸውን ነው፡፡ ለዚህም አንዱ አብነት፣ ቢሮአችን ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ ድረገጽ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በማንኛውም ቦታና ጊዜ በሚኖራችሁ ቆይታ ተደሰቱ፡፡ ከቤተሰቦቻችሁና ከጓደኞቻችሁም ጋር ቶሎ ተመልሳችሁ ኑ፡፡ በድጋሚ፣ ለሁላችሁም በአዲስ አበባ አስደሳች ጊዜ እመኝላችኋለሁ፡፡